ራስ መኰንን
ከWikipedia
ልዑል ራስ መኰንን የሸዋ ንጉሥ የነበሩት የሣህለ ሥላሴ ልጅ የልዕልት ተናኘወርቅ እና የደጃዝማች ወልደሚካኤል ልጅ ናቸው። ግንቦት 1 ቀን 1844 ዓ.ም ጎላ ወረዳ ደረፎ ማርያም በሚባል ሥፍራ ተወልደው፤ እስከ 14 ዓመት ዕድሜያቸው ከአባታቸው ጋር ከኖሩ በኋላ ያጐታቸው የንጉሥ ኃይለ መለኮት ልጅ ዳግማዊ ምኒልክ ገና የሸዋ ንጉሥ እንደነበሩ፡ ወደርሳቸው ቤተመንግሥት መጥተው፡ ባለሟል ሆኑ።
በ1868 ዓ.ም ዕድሜያቸው 24 ዓመት ሲሆን ከወይዘሮ የሺ እመቤት ጋር ተጋብተው ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም የወደፊቱን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ወለዱ።
ልዑል ራስ መኮንን የንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ምኒልክ ተወካይ ሆነው ሁለት ጊዜ የአውሮፓን አገሮች ጎብኝተዋል። በዚህ ጊዜ እሳቸው ኢጣሊያን ሲጎበኙ በነበረ ጊዜ የኢጣሊያ ጋዘጦች የውጫሌ ውልን በተመለከተ፤ "...በውጫሌ ውል ላይ ኢትዮጵያ የኢጣሊያን ጥገኝነት ተቀብላ ውል ከፈረመች በኋላ የጀርመን ንጉሠ ነገሥት ከኢትዮጵያ የሚላከውን ማንኛውንም ደብዳቤም ሆን ጉዳይ በኢጣሊያ መንግሥት በኩል መቀበል ሲገባቸው በቀጥታ ከምኒልክ የተጻፈውን ደብዳቤ ተቀብለዋል..." እያሉ የጻፉትን ራስ መኮንን ተቃውሞአቸውን ለኢጣሊያ መንግሥት ከነገሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የውሉን መበላሸት ለአጤ ምኒልክ አሳወቁ። ከኢጣሊያንም ጋር በተደረገውም ጦርነት ራስ መኮንን 15000 እግረኛ ወታደሮች ይዘው ከምኒልክ እና ታላላቅ ጦር አዛዦች ጋር ዘምተዋል።
በ1898 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በብርቱ ስለታመሙ ለኅክምና ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ ጥር 4 ቀን ከከተማቸው ከሐአረር ተነሱ። ጥር 9ቀን ቡርቃ ወንዝ አድረው የጥምቀትን በዓል አክብረው ከዋሉ በኋላ ሕመሙ ስለጸናባቸው ወደ ኋላ ተመልሰው ቁልቢ ገብተው በሐኪም ይታከሙ ጀመር። እዚሁም ሲታመሙ ከቆዩ በኋላ መጋቢት 13 ቀን 1898 ዓ.ም ቁልቢ ላይ አርፈው ሐረር ላይ እሳቸው በተከሉት በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ። ዐፄ ምኒልክም የአርባቸው ለቅሶ የሚለቀሰው አዲስ አበባ እንዲሆን ባዘዙት መሠረት፤ ሰኞ ሚያዝያ22 ቀን በአዲስ አበባና በዙሪያው ያሉት የየገዳማቱና የየአድባራቱ ካህናት የክርስቲያን የፍታት ጸሎት ተድርጎ በማግስቱም ማክሰኞ የጊዮርጊስ ዕለት ሚያዚያ 23ቀን 1898 ዓ.ም በሰኢ ሜዳ ላይ ድንኳን ተተክሎ፤ መኳንንቱና ሠራዊቱ ተሰብስቦ የራስ መኮንን የማዕረግ ልብሳቸውና የራስ ወርቃቸው፤ ኒሻኖቻቸውና የጦር መሳሪያቸው ተይዞ ፈረስና በቅሏቸው በወርቅ እቃ ተጭነው በሠራዊቱ መካከል እየተመላለሱ ታላቅ ልቅሶ ተለቀሰላቸው። ከአልቃሾቹም አንዱ ደግነታቸውን ለማስታወስ እንዲህ ብሎ አሟሸ፤- ስልከኛው ሲያረዳ ነገር ተሳሳተው፤ መኮንን አይደለም ድኃ ነው የሞተው
[ለማስተካከል] ዋቢ መጻሕፍት
- ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ - ቀ.ኃ.ሥ 1929ዓ.ም - ገጽ 1፣ 2፡ 9-10
- አጤ ምኒልክ - ጳውሎስ ኞኞ 1984 ዓ.ም ገጽ 143፤ 160