ኢትዮጵያ
ከWikipedia
|
|||||
የሥራ ቋንቋ | አማርኛ | ||||
ዋና ከተማ | አዲስ አበባ | ||||
ፕሬዝዳንት | ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ | ||||
ጠቅላይ ሚኒስትር | መለስ ዜናዊ | ||||
የመሬት ስፋት | 1,127,127 ካሬ ኪ.ሜ. (ከዓለም 26ኛ) | ||||
የሕዝብ ብዛት | 73,053,286 (ከዓለም 16ኛ) | ||||
ገንዘብ | ብር | ||||
ብሔራዊ መዝሙር | ወደፊት ገስግሺ ውድ እናት ኢትዮጵያ |
ኢትዮጵያ በኣፍሪካ ቀንድ የምትገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት። ድሮ አቢሲኒያ በሚል መጠሪያ ትታወቅ ነበር። በአፍሪካ ነፃነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ከቻሉ ሁለት አገሮች አንዷ ነች። የታሪክ ሊቃውንት ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪክ መወረሱን እና ትርጕሙም «በፀሓይ የከሰለ ገጽ» ማለት እንደሆነ ይገልጻሉ። ቀደምት የኢትዮጵያ ሊቃውንት ግን ይህን አይቀበሉትም። ስያሜው የአክሱም መሥራች ከነበረው «ኢትዮጲስ» እንደተገኘ፤ እርሱም የኩሽ ልጅ፣ (የካም የልጅ-ልጅ፣ የኖህ የልጅ-ልጅ-ልጅ) እንደነበር ይተርካሉ።
ይዞታ |
[ለማስተካከል] ታሪክ
የአክሱማውያን ስፈን በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ጠንካራ መንግሥታዊ ማኅበረሰብ ነበር። በፋርስ፣ ሮማ እና ቻይና ይገኙ ከነበሩ ታላላቅ መንግሥታት በወደረኛነት የሚቈጠር ትልቅ ኅይል ነበር። በ6ኛው ምእት ዓመት የአክሱማውያን ግዛታዊ ቍጥጥር የዛሬዋን የመን ግዛት ይጨምር ነበር። ግን በ7ኛው እና በ8ኛው አምኣት የአክሱም ሥልጣኔ በእስልምና መነሣት እና መስፋፋት ተዳክሞ ለውድቀት በቃ። ተከታዩ የዛጔ ሥርወ-መንግሥት ልክ በድንገት እንደተነሣ በድንገት ሲያበቃ፣ ይኵኖ አምላክ ሥልጣን በ1262 ዓ.ም. ጨበጡ፤ እንዲያም ሲል የመጀመሪያው የሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት ዐፄ ሆኑ።
በ1880ዎቹ እ.ኤ.አ. የአውሮፓ መንግሥቶች አፍሪካን በቅኝ ገዢነት ማስተዳደር ጀመሩ። በኢትዮጵያ እና ጣልያን መካከል የነበሩ የዚያ ዘመን ውዝግቦች ወደ አድዋ ጦርነት በ1888 ዓ.ም. አመሩ። በጦርነቱ የጣልያን ትልቅ ዘመናዊ ጦር ትልቅ ሽንፈት የደረሰበት መሆኑ ዓለምን አስደነቁ።
በ20ኛው ምእት ሁለተኛው ሩብ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ኢትዮጵያን መምራት ጀመሩ።
[ለማስተካከል] ሥነ-መንግሥት
[ለማስተካከል] መልክዓ-ምድር
ኢትዮጵያ በሰሜን ምስራቅ አፍረካ ከ3-14 ዲግሪ ሰሜን እና ከ33-48 ዲግሪ ምሥራቅ የምትገኝ አገር ስትሆን የቆዳ ስፋቱዋም 1,127,127 ካሬ ኪ.ሜ. ነው። በሰሜን ከኤርትራ፣ በምዕራብ ከሱዳን፣ በደቡብ ከኬኒያ፣ እንዲሁም በምሥራቅ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያ ጋር ትዋሰናለች። የኢትዮጵያ አብዛኛው ግዛት በተራሮች እና አንባዎች የተሞላ ሲሆን፣ ታላቁ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ እነዚህኑ ከፍተኛ ቦታዎች ከሰሜን ምሥራቅ ወደ ደቡብ ምዕራብ በመጋደም ለሁለት ይከፍላቸዋል። በስምጥ ሸለቆው ዙሪያም በረሃማ የሆኑ ዝቅተኛ ቦታዎች ይገኛሉ። ይሄን መሰሉ የመልክዓ-ምድር ልዩነት አገሪቷ የተለያዩ የአየር ንብረት፣ የአፈር፣ የዕፅዋት እና የሕዝብ አሰፋፈር ገጽታዎች እንዲኖሯት አስችሏታል። በከፍታና በመልክዓምድራዊ አቀማመጥ የተነሣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ዐይነት የአየርንብረት ክልሎች ይገኛሉ። እነርሱም፦
- ደጋ - ከፍታቸው ከባሕር ጠለል 2400 ሜትር የሚጀምር እና የሙቀት መጠናቸው ከ 16 ዲግረ ሴ.ግ የማይበልጥ፤
- ወይናደጋ - ከፍታቸው ከባሐር ጠለል ከ1500 እስከ 2400 ሜትር፣ ሙቀታቸውም ከ16 ዲግረ ሴ.ግ እስከ 30 ዲግረ ሴ.ግ የሚደርስ፣ እና
- ቆላ - ከባህር ጠለል በታች ጀምሮ እስከ 1500 ሜትር ከፍታ ያላቸው፣ የሙቀት መጠናቸውም ከ30 ዲግረ ሴ.ግ እስከ 50 ዲግረ ሴ.ግ የሚደርስ አከባቢዎች ናቸው።
ዋናው የዝናብ ወቅት ከሠኔ አጋማሽ እስከ መስከረም አጋማሽ ሲሆን፣ ከርሱ ቀደም ብሎ አልፎ አልፎ የሚጥል የበልግ ዝናብ በየካቲት እና በመጋቢት ይከሰታል። የተቀሩት ወራት በአብዛኛው ደረቅ ናቸው።
[ለማስተካከል] አስተዳደራዊ ክልሎች
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጽያ ውስጥ 9 አስተዳደራዊ ክልሎች ይገኛሉ። አወቃቀራቸውም በህገመንግስቱ በተደነገገው መሰረት «በህዝብ አሰፋፈር፤ ቋንቋ፤ ማንነት እና ፈቃድ ላይ» ተመስርቶ ሲሆን ክልሎቹም ፦
- የትግራይ ክልል
- የአፋር ክልል
- የአማራ ክልል
- የኦሮሚያ ክልል
- የሶማሌ ክልል
- የቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል
- የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል
- የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል
- የሀረሪ ሕዝብ ክልል ሲሆኑ በተጨማሪም
- አዲስ አበባ እና
- ድሬዳዋ እራሳቸውን የቻሉ የአስተዳደር አካባቢዎች ሆነው ተዋቅረዋል።
[ለማስተካከል] ሕዝብ
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሄረሰቦች የሚገኙባት «የብሄረሰቦች ሙዚየም» ልትሰኝ የምተችል ሀገር ነች። ትልልቆቹ ብሄረሰቦች የኦሮሞ፣ የአማራ፣ እና የትግራይ እንደሁም የሶማሌ ሲሆኑ እነዚሁ ብሄረሰቦች ከጠቅላላው የአገሪቱዋ ሕዝብ ቁጥር ክ3/4ኛ በላይ የሚሆነውን ይይዛሉ። በሃይማኖት በኩልም ሁለቱ ትልልቅ ሃይማኖቶች እስልምና እና ክርስትና በስፋት የሚተዋልባት አገር ናት። እስልምና ከ 40-45% ፡ ክርስትና ከ 35-40% እንዲሁም ሌሎች ከ 10-20% እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
[ለማስተካከል] ቋንቋዎች
በኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች የሚኖሩ ሲሆን በቋንቋም በኩል ከ80 በላይ የሚሆኑ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ሀገር ናት፡፡ በአሁኑ ወቅት በእብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚነገሩት ቋንቋዎች አማርኛ እና ኦሮምኛ ሲሆኑ፤ አማርኛ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ያሉ ነዋሪዎች የመማሪያ፤ የመገበያያ እንዲሁም የስራ ቋንቋ ሆኖ የቆየ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት የብሄራዊ ቋንቋ ነው። በኢትዮጵያ የሚነገሩት ቋንቋዎች ወደ አራት ዋና ዋና የቋንቋ ክፍሎች ሊካተቱ ይችላል። እነዚሁም
- ኩሻዊ፦ ወደ 19 ቋንቋዎችን የያዘ
- የአባይ-ሰሃራዊ፦ወደ 20 ቋንቋዎችን የያዘ
- ኦሞአዊ፦ወደ 23 ቋንቋዎችን የያዘ እና
- ሴማዊ፦ወደ 12 ቋንቋዎች የያዘ ናቸው።
ኩሻዊ ከሚባሉት ቋንቋዎች ዋና ዋናዎቹ ኦሮምኛ፣ ሶማልኛ፣ አፋርኛ፣ ሲዳምኛ፣ ሃዲያኛ እና ከምባትኛ ሲሆኑ ከአባይ-ሰሃራዊ የቋንቋ ምድብ የሚካተቱት በርታኛ፣ ኩናማኛ፣ ጉሙዝኛ፣ ሙርሲኛ እና የመሳሰሉት ናቸው። እንደ ወላይትኛ፣ ጋሞኛ፣ ከፋኛ፣ ሃመርኛ የመሳሰሉት የኦሞአዊ ቋንቋ ዘሮች ሲሆኑ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጉራጊኛ፣ ስልጢኛ፣ ሀደሪኛ እና መሰል ቋንቋዎች ከሴማዊ ቋነቋዎች ይመደባሉ።
የሴሚቲክ ምንጭ ያላቸው እንደ አማርኛ ያሉት ቋንቋዎች የራሱ የሆነ የተለየ የፊደል ስርአት ያላቸው ሲሆን ይህም ኢትዮጵያን ከአፍሪቃ ብቸኛዋ ባለ ጥንት ፊደል ሀገር ያደርጋታል። እነኚህ የሴሚቲክ ምንጭ ያላችው ቋንቋዎች ግዕዝ የተባለ በአሁኑ ወቅት ከቤተክርስትያን ውጭ ለእለት ተእለት ግልጋሎት ላይ የማይውል ግንድ ዘር አላቸው።
[ለማስተካከል] ምጣኔ-ሃብት
[ለማስተካከል] ባህል እና ሃይማኖት
ቀን | የበዓሉ ስም | የበዓሉ ስም በእንግሊዝኛ | አስተያየት |
---|---|---|---|
መስከረም ፩ | እንቁጣጣሽ | Ethiopian New Year | |
መስከረም ፲፯ | መስቀል | Finding of the True Cross | |
ጥቅምት ፳፬ | ኢድ አል ፈጥር | End of Ramadan | ይለዋወጣል፣ ይህ ቀን ለ1998 ዓ.ም. ነው |
ታህሳስ ፳፱ | ገና | Christmas | |
ጥር ፪ | ኢድ አል አደሃ | Eid ul-Adha (Feast of the Sacrifice) | ይለዋወጣል፣ ይህ ቀን ለ1998 ዓ.ም.ነው |
ጥር ፲፩ | ጥምቀት | Epiphany | |
የካቲት ፳፫ | የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል | Battle of Adowa Commemoration Day | |
ሚያዚያ ፬ | መውሊድ (የነብዩ መሃመድ የልደት ቀን) | Birthday of The Prophet Muhammad | ይለዋወጣል፣ ይህ ቀን ለ1998 ዓ.ም. ነው |
ሚያዚያ ፲፫ | ስቅለት | Good Friday (Crucifixion) | ይለዋወጣል፣ ይህ ቀን ለ1998 ዓ.ም. ነው |
ሚያዚያ ፲፭ | ትንሳዔ (ፋሲካ) | Easter | ይለዋወጣል፣ ይህ ቀን ለ1998 ዓ.ም. ነው |
ሚያዚያ ፳፯ | የጀግኖች አርበኞች መታሰቢያ ቀን | Patriots' Day | |
ግንቦት ፳ | ደርግ የወደቀበት ቀን | Downfall of the Derg Regime |
ኢትዮጵያ |
ታሪካዊ ቦታዎች - አክሱም | ላሊበላ | ጎንደር | ነጋሽ | ሐረር | ደብረ-ዳሞ | አዲስ አበባ |
የኢትዮጵያ ከተሞች |
አስተዳደር አካባቢዎች - አዲስ አበባ | ድሬዳዋ |
በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ አገሮች |
ሊቢያ| ላይቤሪያ| ሌሶቶ| የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ| ማሊ| ማላዊ| ማዳጋስካር| ሞሪሸስ| ሞሪታኒያ| ሞሮኮ| ምዕራባዊ ሣህራ| ሞዛምቢክ| ሩዋንዳ| ሱዳን| ሲሸልስ| ሳን ቶሜና ፕሪንሲፔ| ሴየራ ሌዎን| ሴኔጋል| ስዋዚላንድ| ሶማሊላንድ| ሶማሊያ| ቡሩንዲ| ቡርኪና ፋሶ| ቤኒን| ቦትስዋና| ቱኒዚያ| ታንዛኒያ| ቶጎ| ቻድ| ኒጄር| ናሚቢያ| ናይጄሪያ| አልጄሪያ| አንጎላ| ኢትዮጵያ| ኢኳቶሪያል ጊኔ| ኤርትራ| ኬንያ| ኬፕ ቨርድ| ካሜሩን| ኮሞሮስ| ኮት ዲቯ| ኮንጎ ሪፑብሊክ| ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ| ዚምባብዌ| ዛምቢያ| ዩጋንዳ| ደቡብ አፍሪካ| ጅቡቲ| ጊኔ| ጊኔ-ቢሳው| ጋምቢያ| ጋቦን| ጋና| ግብፅ| |