የሕገ መንግሥት ታሪክ
ከWikipedia
የሱመር ከተማ ላጋሽ አለቃ ኡሩካጊና ከ ክ.በ. 2300 ያሕል ዓመታት ያዋጀ ሕገ ፍትሕ በታሪካዊ መዝገብ እስከምናውቀው ድረስ መጀመርያ የሕገ መንግሥት ሰነድ ነው። ሰነዱ እራሱ ገና አልተገኘም፤ ነገር ግን ለዜጎቹ አንዳንድ መብት እንደ ፈቀደላቸው ይታወቃል። ለምሳሌ ለመበለትና ለደሀ አደጎች ቀረጥ እንዳስቀረላቸው ድሆችንም ከሃብታሞች አራጣ እንደጠበቃቸው ይታወቃል።
ከዚህ በኋላ ብዙ መንግሥታት በተጻፈ ሕግ እንዲገዙ ልዩ ስርዓት ነበራቸው። ከተገኙት ሕገጋት ሁሉ ጥንታዊ የሆነው ከክ.በ. ወደ 2050 ዓመት የሚጠጋ የገዙ የኡር ንጉሥ የኡር-ናሙ ሕገጋት ነው። በተለይ ዕውቅ የሆኑ የመንግሥት ሕጎች የባቢሎን ንጉሥ ሃሙራቢ ሕገጋት፤ የኬጢያውያን ሕገጋት፤ የአሦር ሕገጋት፤ ሕገ ሙሴ ለእስራኤል እንዲሁም የፋርስ ንጉስ ቂሮስ ትእዛዛት ናቸው።
ከ ክ.በ. 628፣ ድራኮ የሚባል ጸሃፊ የአቴና ከተማ ሕገጋት ጻፈ፤ ይህም ሕግ እጅግ ጨካኝ ሆኖ ይሙት በቃ ለማንኛውም ጥፋት ወሰነ። ከ ክ.በ. 600፣ የአቴና አለቃ ሶሎን አዲስ ሕገ መንግሥት ፈጠረ። የሰራተኞች ሸክም አቀለለ፣ ነገር ግን ባላባትነት በልደት ሳይሆን በንብረት ብዛት እንዲቈጠር አስደረገ።
የግሪክ ፈላስፋ አሪስጣጣሊስ ክ.በ. 350 የሚያሕሉ ዓመታት የሕገ መንግሥት ሀሣብ ለይቶ ዐወቀ። በመደምደሚያው የተሻለው ሕገ መንግሥት ከንጉሣዊ፣ ከመኳንንታዊና ከሕዝባዊ ወገኖች የተደባለቀ መሆኑን ገመተ። በሀሣቡ በመንግሥት የሚከፋፈሉ ዜጎች ከማይከፋፈሉ ከባርዮችና ዜጎች ካልሆኑ ሰዎች ልዩነት አደረገ።
ሮማውያን መጀመርያ "12ቱ ሰንተረዦች" የተባለውን ሕገ መንግሥት ያወጡ በ457 ክ.በ. ነበር። ከዚያ በኋላ አንዳንዴ የተለያዩ ሕጎችና ትእዛዛት ይጨምሩበት ነበር እንጂ እስከ መጽሐፈ ቴዎዶስዮስ ድረስ (430 ዓ.ም.) ሌላ ክምቹ ሕገ መንግሥት አልኖረም ነበር። በኋላም በምሥራቁ መንግሥት (ቢዛንታይን) በኩል መጽሐፈ ዩስጢኒያኖስ (526 ዓ.ም.) ለአውሮፓ ከፍ ያለ ተጽእኖ ነበረው። ይህም በምስራቁ ነገሥታት 3ኛ ሌዎን ኢሳውራዊ "ኤክሎጋ" (732 ዓ.ም.) እና በ1ኛ ባሲሌዎስ "ባሲሊካ" (870 ዓ.ም.) በተባሉት ሕገ ፍትሐን ተከተለ።
ከምዕራቡ ሮማ መንግሥት ውድቀት ደግሞ ወደ ተረፈው ሕዋእ ውስጥ ከፈለሱት ጀርመናውያን ወገኖች አብዛኛው የራሳቸውን ሕጎች ዝርዝር በጽሑፍ አወጡ። በተለይ የሚታወቁም የቪዚጎቶች አለቃ ዩሪክ ሕግ (463 ዓ.ም.)፣ የቡርጎንዳውያን ሕገጋት (እኚህ ለጀርመናውያንና ለሮማውያን የተለያየ ፍትሕ ነበራቸው)፣ የአላማናውያን ሕገጋትና፣ የፍራንኮች ሕገጋት ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ የተጻፉት ከ492 ዓ.ም. ጀምሮ ነው። በ498 ዓ.ም. የቪዚጎቶች አለቃ 2ኛ አላሪክ መጽሐፈ ቴዎዶስዮስና አንዳንድ የተለያዩ የቀድሞ ሮማ ሐገጋት አከማችተው አዋጁአቸው። ከዚህም በኋላ የታዩ ሕጎች የሎምባርዶች ሕገጋት (635 ዓ.ም.)፣ የቪዚጎቶች አዳዲስ ሕገጋት (646 ዓ.ም.)፣ የአላማናውያን አዳዲስ ሕገጋት (722 ዓ.ም.) እና የፍሪዝያውያን ሕገጋት (777 ዓ.ም.) አሉ።
በ596 ዓ.ም. በጃፓን 17 አንቀጽ ያለ ሕገ መንግሥት በልዑል ሾታኩ እንደተጻፈ ይታመናል። እንዲሁም በ614 ዓ.ም. ከነቢዩ መሐመድ የወጣው የመዲና ሕገ መንግሥት ዕጅግ ጥንታዊ ምሳሌ ነው።
በስሜን አሜሪካ የኖሩ ኗሪ ጎሣ ሆደናሾኔ 'የአፈ ቃል' ሕገ መንግሥት "ጋያናሻጎዋ" የነበራችው ከ1080-1140 ዓ.ም. አካባቢ ጀምሮ እንደሆነ ይታመናል። አንዳንድ ምሁር ይህ ሕግ በከፊል ለአሜሪካ ሕገ መንግሥት ተጽእኖ እንደነበረው እናመናለን ባዮች ናቸው።
በእንግሊዝ አገር በ1092 ዓ.ም. ንጉስ 1 ሄንሪ የነጻነት ሥርአት የተባለውን ሰነድ አዋጀ። ይህ መጀመርያ የንጉሱን ሥልጣን ወሰኖ ንጉሡ ለቤተ ካህናትና ለቤተ መሳፍንት ወገኖች የሚገባውን እንቅብቃቤ ገለጸ። ይህም መሰረት በመኳንንቱ ሲዘረጋ በ1207 ዓ.ም. የእንግሊዝ ንጉሱን ዮሃንስ (ጆን) ማግና ካርታ ("ታላቅ ሥርዓት") የሚባለውን ሰነድ እንዲፈርሙት አስገደዱዋቸው። ከዚሁ መሃል ቁም ነገር የሆነው ንጉሡ ያለ ሕጋዊ ሂደት ማንንም ሰው እንዳይገድሉ፣ ከአገር እንዳያሳደዱ፣ ወይም እስር ቤት እንዳያስገቡ ከለከላቸው። በዚያ ወቅት ያ ሰነድ በእንግሊዝ አገር የነጻነት መሠረት ሆነ።
በ1212 እና 1222 ዓ.ም. መካከል አንድ የሳቅሰን አስተዳዳሪ አይከ ቮን ረፕጎቭ ያቀነባበረው ሕገጋት ሳቅሰንሽፒግል በአንዳንድ ጀርመን ክፍላገር እስከ 1892 ዓ.ም. ድረስ ላይኛ ሕገ መንግሥት ሆነ።
በ1228 ዓ.ም. ሱንዲያታ ከይታ ማሊ መንግሥትን ለማወሐድ የ'አፈ ቃል' ሕገ መንግሥት አወጡ። ይህ ሕግ 'ኩሩካን ፉጋ' ተብሎ ነበር።
በ1240 አካባቢ በግብጽ አገር ቅብጡ አቡል ፋዳዒል እብን አል-አሣል ፍትሐ ነገሥት በአረብኛ ጻፉ። እብን አል-አሣል ሕጎቹን የወሰዱት በከፊል ከሃዋርያት ጽህፈቶችና ከሕገ ሙሴ፤ በከፊልም ከድሮ ቢዛንታይን ነገስታት ሕጎች ነበር። መጽሐፉ በግዕዝ ተተርጉሞ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ወቅት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በ1450 አከባቢ እንደነበር የሚል ታሪካዊ መዝገብ አለ። ቢሆንም መጀመርያ እንደ ሕገ ምንግሥት መጠቀሙን የተመዘገበው በዐፄ ሰርሰ ድንግል ዘመን (ከ1555 ጀምሮ) ነው። ፍትሐ ነገስት እስከ 1923 ዓ.ም. የብሄሩን ዋና ሕግ ሆኖ ቆየ።
በ1904 ዓ.ም. ዐጼ 2 ምኒልክ የዘመናዊ ሕገ መንግሥት ፅንሰ ሀሳብ ተረድተው በጸሀፊው መምሬ ብስራት አንድ ሕገ መንግሥት የሚመስል ሰነድ ታተመ፤ ይህ ግን በውነት ሕገ መንግሥት አይባልም። "በምኒሊክ ስለተቋቋሙት ሚኒስቴሮች በምሳሌ የቀረበ ጽሑፍ" በምሳሌና በትርጓሜ የእያንዳንዱን ሚኒስቴር ሥራ እንደ ሰውነት አካላት አስመሰለ። ለምሳሌ፦
- "የራስ ሥራ - በነፍስና በስጋ ባጥንትና በዥማት ተዋደው በሚኖሩ አካላት ሁሉ አለቃና የውቀት መሰብሰቢያ ሳጥን ነው...
- የዦሮ ሥራ - ዦሮ በትምህርት የሚገኘውን ጥበብና ዕውቀት ሁሉ ከራስና ከልብ ለማዋሐድ የድምጽ ኃይል የሚስብ መኪናነት አለው። ዦሮ ባይኖር ዕውቀትና ፍሬ ያለው ንግግር ባልተገኘም ነበር...
- ያይን ሥራ - ዓይን ለማየት ከብርሃን ጋራ ተስማምቶ የተፈጠረ ያካላት ሁሉ መብራት ነው። በጅና በግር ለሚሠራ ሥራ በትምህርት ለሚገኝ ጥበብ ሁሉ መሪ ነው። ግዙፍ ሆኖ የተፈጠረውን ፍጥረት ሁሉ ለማየት ይችላል...
- የልብ ሥራ - ልብ የደግና የክፉ ሃሳብ መብቀያ ነው...
- የጅ ሥራ - እጅ በጥበብ ለተገኘ ሥራ ሁሉ የብረትና የናስ የወርቅ ፋብሪካና መኪና በያይነቱ፤ የርሻ የጽሀፈት የስፌት የቤት ሥራ በያይነቱ፤ ይህን ለመሰለ ሁሉ ሠራተኛ ነው...
- የግር ሥራ - እግር ለነዚህ ለተቆጠሩት ሁሉ መቆሚያ ጉልበትና ብርታት ልብ ወደ አስበበትና ወደ ታዘዘበት መሄጃ ነው..."
የሚመስል ቋንቋ በውስጡ አለበት።
ኢትዮጵያ መጀመርያ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት የተቀበለችው በ1923 አመተ ምኅረት በአጼ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የታወጀ ሲሆን የሕግ አማካሪ ቤቶች በሁለት ያስከፈለ ነው። ይህ የመንግሥታቸው ዋና መሠረት ሆኖ እስከ 1948 አ.ም. አገለገለ፤ በዚያ አመት ተሻሽሎ በወጣ ሕገ መንግሥት ሕዝቦች በመንግሥት ሥራ የሚጫወቱት ሚና እንደገና ተስፋፋ። ይህ ብቻ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ሆኖ እስከ 1967 አ.ም. ቆየ፤ የዛኔ በደርግ በግፍ (በሕገ መንግስት እራሱ ባልሆነ ሂደት) ተሰረዘ።